ይድረስ ለጠቅላይ ምንስትር ዶር ዓቢይ አህመድ!
ክቡር ጠቅላይ ምንስትር በአባይን ወንዝ የሕዳሴ ግድብን የመጀመሪያውን የመሙላት ስርአተድርጊትን በተሳካ መንገድ በመጠናቀቁ ደስ ያላለው ኢትዮጵያዊ የለም። የኢትዮጵያ ሕዝብም ደስታም ወደር የለውም።
ለመሆኑ በአሁኑ ሰአት የአባይ ወንዝ ምን ስሜት እንደሚሰማውና እንዴት ከራሱ ጋር የሕዳሴን ጥንስስና ብስራት እንደሚቃኝ ያውቃሉ?
አባይ ከኔ ጋር ትውውቅና ዝምድና የጀመረው ከሦስት አስርተ ዓመት በፊት ነው። ይህም የሆነው በወጣትነት ጊዜዬ የአዲስ አበባ የ፲፬ አመት የቅርጫት ኳስ ተጨዋች ተመርጬ ወደ ባሕርዳር በሄድኩበት ወቅት ነበር። አባይ ሲያዪት ያማረ ሲቀርቡት ያጠመቀ የማይሳሳና ፀጋውን ለማንም ሳያዳላ አሳልፎ የሚሰጥ የዋህ ፍጡር ነው።
ይህ በኔና በሱ የተፈጠረው ጥልቅ ትውውቅ አባይን ፏፏቴውን ሲወርድ እንደሚያሰማው ድምፅ ሞገድ ባይሆንምና አባይም ምንም ቃላት አውጥቶ በፈለገው ቋንቋ ሊያስረዳን ባልችልም በአሁን ጊዜ በአእምሮው ውስጥ የሚያነበንበውን ጥዋኔ በእኔ አድሮ የሆዱን አውጥቶ እንድነግርለት መልእክቱን አስፍሯል።
እናም ይህችን “እስከመቼ? የአባይ ወንዝ የራስ ሙግት፣ ከህዳሴ እስከ ትንሣኤ” የምትለውን መድብሌን ላካፍልዎት ወድጃለሁ።
እንደእግዚአብሔር ፈቃድ ወደፊት የህዳሴ ግድብ ስራ ሊጀምር በሚመረቅበት ጊዜ በቦታው ተገኝቼ የአባይን የእራስ ሙግት በቃሌ እንዳሰማም ተስፋ አለኝ።
በተጨማሪም እነዚህ ቃላቶች በህዳሴ ግድብ በአንድ ግድግዳ ተፅፈው ለመጪው ትውልድ ይቅሩ ዘንድ ምኞቴ ነው።
አመስግናለሁ።
ኢትዮጵያ ለዘለአለም ትኑር
|||||||||||||||||||||||||||||||||||||||||||||||||||||||||||
…. የአፈጣጠሬ ስልት ….
በለምለሟ አገር በኢትዮጵያ ምድር
ማንም ሳያልመኝ ማንም ሳይወስነኝ
ተወለድኩ ከጣና ምድር ስትፈጠር
ልኖር ለዘላልም ጊዜም እንዳይሽረኝ
አንድ ልጇ ሆኜ ልጠራ በስሜ
አስጠመቁኝ እኔን አባይ ብለው ስሜን።

…. ማናለብኝነቴ ….
ከቤቷ ወጣሁኝ ላልመለስ ብዬ
አልሞላኝ አቅምአዳም ስወጣ ከቤቷ
አቤት ችኮላዬ ይደንቃል ፍጥነቱ የጉርምስናዬ
ያወጣጤ ከቤት መንገድ አካሄዴ
ሳልጦራት ሳልበጃት ምንም ሳልሰራላት
ላልመለስ ብዬ ወደኋላም ላላይ
አሻፈረኝ ብዬ ወጣሁ እንደቀረሁ።
ያላትን ርስቷን ማእድኗን ወስጄ
አከፋፈልኩባት ሳልሳስት ለቤቷ
እንዳልወለደችኝ እንዳላሳደገችኝ
ሁሉን እያለማሁ እያበለፀኩኝ
ሳልስናበታት እሷን ትቼ ሄድኩኝ።
ውለታ አልተከፈለኝ ወይ አልተመስገንኩ
በሄድኩበት ሁሉ ተይዤ ታስሬ
ክረምት አልል በጋ ፀደይ ወይስ መከር
ሁሉን እያለማሁ ምግብ አኖራለሁኝ
የህይወት እስትንፋስ ሁሌም እሰጣለሁ።
ወልዳም አልጣለችኝ አንቅራአልተፋችኝ
እምብርቷላይ ተክላ አለቅም አለችኝ
የልጅነቴንም ዘላለማዊዉን ፕላሴንታዉንም
ምንሊበጃት ይሆን እንዲህ ያለ ፍቅር
እቅፍ ጭምቅ ኣርጋ ብላኝ የበኩሬ
እኔ አልታየኝም ይህም ታላቅ ፍቅሯ
የናትነቷ ምንጭ የማይደርቅ ተግባሯ።
… የተምሳሌትነት ጥንሥሥነቴ …
ብዬ እስከመቼ ሳስብ ሳወላውል
ኃይልዬ አሰበኝ መክሮም ቀመረኝ
አባይ አለኝ እሱም በስሜ ተጣርቶ
ወደፊት መገስገስ ላንተ የተሰጠ ነው
እንዳትቆም ሰርቶሃል እንዳትሽመደመድ
ትሄድ ዘልቀህ አልምተህ አቋርጠህ አፍሪካን
የተፈጥሮ ብቃት እንዲሁም ግድ ነው።
ከዚያም በመቀጠል ትንፋሹን ሰብስቦ እንዲህ ተናገረኝ
ፈጣሪ ሲልልን ቀንም ሲወጣልን
አይዞህ ልጄ አንድ ቀን ትመጣለህ ቤትህ
እንደጠፋው ልጅም ደግመህ ትገኛለህ
ትቀበልሀለች እጆቿን ዘርግታ ያላንዳች እርዳታ
ትንከባከብሃለች ማረፊያ ፈልጋ
አንተ ብቻ ታገስ ሰከን ብለህ ንጐድ
ሕዝቧን ታበልፅግ ዘንድ ብርሃን ትሰጥ ዘንድ።
…. ውለታ ….
ይህን ሃሳቤን ሳሰላስል ቀኔን
ትዝ አለኝ ያ ቃሌ የገባሁላትን
ጉዞዬን ስጀምር ገና ዱሮ ሳለ
ተመልሼ አልመጣም ብዬ ሳረጋግጥ
ሰጠኋት ማላዬን ቆምብዬ ልሰማት
ቦታም ከሰጠችኝ ዘና ብዬ ላያት
ጊዜንም ወስጄ ከልቤ ካንጀቴ ላገለግልላት።

… ሕዳሴ …
ይህን ተስፋን ይዤ ስመልስ ስመለስ
ቀኔ ተቆረጠ የመመለሴ እለት
ሕዳሴ ነው አሉኝ የምመለስ እለት
ኢትዮጽያዊዉ ሁሉ እልል ብሎ ፈካ
ደስታው የኛ ነው ሲል እኔ አለሁኝ አለ።
የእናቴ ድምጿ በአለም ተሰምቶ
የሕዳሴው ዜና ደስታው አስተጋብቶ
አልበቃም ባገር ቤት ሞልቶ ባለምዙሪያ
ባውሮፓ፣ ባሜሪካ፣ በስያና ባውስትራሊያ።
ያለማት ዲያስፖራ ደስታቸው መጣና
ብለው አበሰሩ እልል እልል አሉ
እኔም እኔም አሉ ክንዶች ዘረጉና
ቆመው አስተዋሉ እምባም አነቡና
የሮጠው ልጃችን አሁን ሊሰክን ነው
የተስፋ ብርሃን ሊያጎናፅፈነው
ቃልም እንገባለን በአህጉራት ዙሪያ
የብልጽግናውን ለግንባታው ስራ።
… ብሶትና ተሥፋ …
እኔም ተገረምኩኝ አሁን ምን ስርቼ
እንዲህ ተሞገስኩኝ ምንም ባልተጋሁኝ
ያላትን ሀብት ሁሉ ይዤ በጠፋሁኝ?
የህይወቴ ትርጉም ወደፊት ሩጫ ያገኙትን መጫን
ማን ገባ ፣ ወረደ ወይስ ማን ጎደለ
ሁሌ ችኮላ ነው ማጥፋት ወይም ማልማት
መቆምማ ለኔ ህልም ነው ወይ ዘበት
እኔ አላወኩም ወይ አላገናዘብኩም
የጥንት የጠዋቱን የአባቶችን ተረት
ይወጣዋል እርጎ ከረጋ ወተት።
መንገዴም እረጅም እጅግ ጠመዝማዛ
በደንብ አሰብኩበት አሰላሰልኩኝም
የቱጋ ቆም ብዬ በሰፊው ተኝቼ
እናቴም ስጠራኝ አቤት አለሁ ስላት
የምትፋልገውን ሥራም ሰርቼላት
የብልፅግናዋንም አብይ ብሆንላት
የብርሃኗንም መስረት ሆኜላት
አካባቢዋንም ሳላባክንባት
ለትውልድ የሚተርፍ ዘላቄታዋንም አስተማምኜላት
ባረንጓዴአሻራ በልፅጋ እንዳያት
ያላትንም ንብረት ሳልዘራርፍባት
ደህናደሪ ብዬ ተሰነባብቻት
እራስ ወቃሽነት ሳያብከነክነኝ
ጎረቤቶቿንም ሳላሳዝንባት
ሰላም እሰጣለሁ በየደረስኩበት
ሁሉን ሳላዳላ አበለፅጋለሁ በሄድኩበት እለት።
… ተግባረ ሕዳሴ ….
ኢትዮጵያዊዉ ህዝቤም ማረፊያን ሰራልኝ
ችኮላ ሳይኖረኝ ተደላድዬለት እርፍ እንድልለት
ገንዘብ አበድሩኝ ወይም እርዱኝ ሳይል
አትሥራ አትገንባ በሰሜን ቢቦልል
ቢያቅራራ ቢፎክር ቢያሰናክል ግንቡን
አድምቆ ገነባው ከሁሉ አስበልጦ
እንድትሆን ኢትዮጵያን ብልፅግና ተምሳል
አደለም ለራሷ እንድትበቃም ላለም።
ክረምቱም ገባና ሃምሌም ነገሰና
ቤትለምቦሳ አሉኝ ሳሎን ግባሉና።
ምንም ወፍራም ብሆን ባምሌ በነሃሴ
ደላ ብሎኝ አረፍኩ ሳሎኑንም በቂ ነው፤
ደሞ አረፍ ብሎ እንዴት ናችሁ ብሎ
ያለኝን ጉልበቴን አጠረቃቅሜ
ጫን ጫን ብዬ ብርሃኔን ቀምሬ
ውለታን ሰርቼ እሷን አስደስቼ
ደህናዋሉ ብዬ መሄድ አያቅተኝ
አደለም ለናቴ እተርፋለሁ ላለም
ብሄድም ለጊዜው ሳሎኑ ቢጠበኝ
ደሞም እተኛለሁ ጊዜዬን ወስጄ
ሲሰፋ ሲገበር ዋናው መኝታዬ።
አሁን ገባኝ እኔ ሰከን ብሎ መሄድ
ደላ ብሎኝ ሣርፍ ባዲሱ ጎጆዬ
እናቴን ስረዳት ከማቅ ሳላቅቃት
ብርሃኗን ስድረው መረቧን ሳሰግረው
ይታየኛል እኔ ወደፊት ስትሄድ
በነፃነት ሳይሆን ወይ ባትንኩኝነት
ሆና ትገኛለች የብልፅግናንም ያፍሪካ ተምሳሌት።
… የወደፊት ልማት …
እሰጣለሁ ምክሬን ለታናናሾቼ
ላዋሽ ለነዝዋይ ለውዱ ተከዜ
ለግቤ ለወይብ ለባሮና ኦም እንዲሁም ሸበሌ
ለዳዋ ለአንገረብ ለመረብ ገናሌ
የናንተ መቸኮል አይበጅም ለእናቴ
ተረጋጉ እናንተም ፈልጉ ማረፊያ
አብዙላት ብርሀኗን አረንጓዴም አርጓት
እናንተም አኑሩ የራስ ድርሻችሁን
ተቋደሱ እናንተም ከውዳሴው ሙሌት
ብልፅግና ያምራል ሲሰራ በራስ ቤት
የባዳ ግልምጫን ሳታይ እናታችን
ደስብሏት ሁልግዜም በልጆቿ ህድር
ሰላሟም በዝቶላት ብልፅግና ሰፍኖ
ልምላሜዋ አምሮ ለትውልዷ ዘልቆ
እንድትሆን ቁሙ ትጉ ለዘላለም።
….. ትንሣዔ …..
አስፉልኝ ግድቡን እኔም ቸኩያለሁ
አልልም በከንቱ እስከመቼ ድረስ
ብድሬን ልመልስ እውን ላርገው ህልሜን
ላብዛላት ሕዳሴን ላስፋው አሻራዬን
ትንሤኤሽ ይበሰር ይነገር ባለም ላይ
እንድትሆኝ ሳይሽ በልጽገሽ ደስ ብሎሽ
ማየት ፈልጌአለሁ በማታ ብርሀን
ማድረግም እሻለሁ እናቴ ኢትዮጵያን
የሰማይ መቀነት የእንተሰላም ገነት
የብልፅግና ማእበል የአፍሪካ ኩራት
ቃልም እገባለሁ ይህንንም ላደርግ
በህይወት እስካለሁ ስኖር ለዘለአለም።
…. የሰላም መልክትኛ ….
ይህን ካደረኩኝ እኔም የድርሻዬን
አላፍርም ዘንድሮ ምን አሉኝ አልልም
ወይስ እስከመቼ ብዬም አላስብም
ደረቴን ነፍቼ እሄዳለሁ እኔም
አሻራዬን ጥዬ ብልፅግናን ምሼ
መብቷን አስጠብቄ ሁሌም አስከብሬአት
አስጠራታለሁኝ ኢትዮጵያን ባለም ላይ
አጠፋለሁ ሳልል የስውልጅ ህይወትን
ሳላስብ ላንዳፍታ ሁሌም እነጉዳለሁ
ጎረቤቶቿንም አስማማቸዋለሁ
የሰላም እምቢልታ በስሟ እነፋለሁ።
ቴዎድሮስ ጉዳይ
ማክስኞ ሐምሌ 21, 2012
July 28, 2020
